20/08/2024
የሞት ቅጣት የሚወሰንበት እና የሚፈፀምበት ሁኔታዎች
=========================
1. መግቢያ
በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ወንጀልን ከመከላከል እና የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ በዚህ መሰረት ሰዎች በእውቀት ማነስ ምክንያት ጥፋት እንዳይፈጽሙ እና በወንጀል እንዳይጠየቁ ለማድረግ ወንጀል የሆኑና የተከለከሉ ተግባራት እንዲያውቁት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ሰዎች ካላቸው ያላግባብ የመጠቀም እና ሌላውን የመጉዳት ሀሳብ ወይም ቸልተኛነት በሚመነጭ ተግባር ክልከላውን ተላልፈው ወይም በህግ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች ባለመወጣት የወንጀል ህጉን ጥሰው ሲገኙ እርምት መውሰድ ዋነኛው አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በወንጀል ህጋችን ላይ በወንጀል የሚያስቀጡ ህገወጥ ተግባራት ተዘርዝረዋል ለእነኚህም የወንጀል ድርጊቶች እንደየወንጀሉ ባህሪ እና ክብደት በተበዳይ፣ በህዝብ እና በመንግስት ላይ ሊያስከትል ከሚችለው የጉዳት መጠን አንጻር የተለያዩ የቅጣት አይነቶችን አስቀምጧል፡፡ በ1996 ዓ.ም የወጣዉ የወንጀል ህግ አንቀጽ 90 እና ተከታዮቹ መሰረት በሀገራችን ህግ ስርዓት እውቅና ያገኙት መደበኛ የቅጣት አይነቶች የሞት፣ የእስራት፣ የመቀጮ እና የግዴታ ስራ ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል ባይደነገጉም በህጉ ጠቅላላ ክፍል የተመለከቱት ሁኔታዎች ተሟልተው በተገኙ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆኑ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ማስጠንቀቅያ፣ ወቀሳ፣ ተግሳጽ፣ ተበዳይን ይቅርታ ማስጠየቅ እና የወንጀል አድራጊውን የተለያዩ መብቶች መሻር የሚያካትቱ ተጨማሪ ቅጣቶች የወንጀል ህግ አንቀጽ 121 እና ተከታዮቹ ተደንግገዋል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ከመደበኛ የቅጣት አነቶች ዉስጥ ስለሞት ቅጣት ምንነትና አፈጻጸም የምንመለከት ይሆናል፡፡
2. የቅጣት ምንነት፣ አስፈላጊነት/አላማ እና አይነት
ቅጣት ወንጀል መፈጸማቸው በፍርድ ቤት በተሰየመው ችሎት ፊት ቀርበው በተሰሙ ምስክሮች ወይም በቀረቡ ማናቸውም ማስረጃዎች በተረጋገጠ እና ፍርድ ቤቱ የጥፋተኛነት ውሳኔ በሰጠባቸው ሰዎች ላይ በዳኞች የሚተላለፍ የእርምት እርምጃ ነው፡፡ ቅጣት የተከለከሉ ድርጊቶችን በማድረግ ወይም ማድረግ ግዴታ የሆኑትን ባለማድረግ የወንጀል ህጉን የተላለፉ ሰዎች ላይ የሚጣል የእርምት እርምጃ ሲሆን አላማውም ወንጀል አድራጊዎችን ማስተማር እና ድጋሚ ሌላ ወንጀል እዳይፈጽሙ ለማድረግ እና ሌሎችም በሌሎች ላይ የተወሰነውን ቅጣት በማየት ወንጀልን ከማድረግ እንዲቆጠቡ ለማድረግ ነው፡፡
ቅጣት ወንጀል አድራጊዎችን በማስተማር መልካም ዜጋ እንዲሆኑ እና ካለፈው ጥፋታቸው ትምህርት ወስደው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ወንጀልን የሚጠየፉ እና ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሰዎች በህግ የበላይነት ከመገዛት ይልቅ አሸናፊነታቸውን በመጠቀም በሌሎች ላይ ተጽዕኖዎችን ማድረሳቸው እና ጉልበት የሌላቸውን ሰዎች መብቶች በመጣስ በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳያብብ እና ከስጋት ያልጸዳ ኑሮን እንዲኖሩ መንገድ ይከፍታል፡፡
3. ከወንጀል ህጋችን አንቀጽ 1 እንደምንረዳዉ ቅጣት የሚከተሉት አላማዎች አሉት፡፡ እነዚህም ፡-
1. ማስተማር (deterrence)
2. መቅጣት (retribution)
3. ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል (prevention, incapacitation, disabling) እና
4. ማረም (reformative, rehabilitation) ናቸዉ፡፡
እነኚህ ከላይ የተዘረዘሩት አላማዎች አካሄዳቸው ወይም እሳቤያቸው ይለያይ እንጂ የመጨረሻ ግባቸው ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የቅጣት አይነቶች የሞት፣ የእስራት፣ የመቀጮ እና የግዴታ ስራ እንዲሁም ማስጠንቀቅያ፣ ተግሳጽ፣ ተበዳይን ይቅርታ ማስጠየቅ እና የወንጀል አድራጊውን የተለያዩ መብቶች መሻር ሊሆን ይችላሉ፡፡
የሞት ቅጣት ታሪካዊ ዳራ
የሞት ቅጣት ሕጎች ቀደምት ታሪክ የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን እሱም በባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ ኮድ (የሃሙራቢ ህግ/ኮድ) ውስጥ ይገኛሉ። በዓለም ላይ የመጀመሪያው የተመዘገበው ግድያ (የሞት ቅጣት) የተፈፀመው በጥንቷ ግብፅ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2627 ዓመተ አለም ነዉ፡፡ የሞት ቅጣት በመካከለኛው ዘመን በስፋት ይሠራበት የነበረና ብዙ ጊዜ በመንግስት ወይም በቤተክርስቲያን ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን ለመቅጣት የሚያገለግል ነዉ፡፡
በታሪክ ውስጥ የሞት ቅጣት በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ውሏል። እንደ ግድያ፣ የሀገር ክህደት እና ስለላ የመሳሰሉ ወንጀሎችን ለመቅጣት ጥቅም ላይ ውሏል። በተጨማሪም እንደ መናፍቅ ወይም ክህደት (heresy or apostasy) ላሉ ሀይማኖታዊ ጥፋቶችም እንደ የቅጣት አይነት አገልግሏል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ የሞት ቅጣት እንደ ስርቆት ያሉ ቀላል ወንጀሎችን ለመቅጣት ጥቅም ላይ ውሏል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ዉስጥ የሞት ቅጣትን ለማስወገድ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በዚሁ መሰረት ብዙ አገሮች ይህን አንቅስቃሴ አስቀጥለዋል፡፡ ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ እ.ኤ.አ በ1786 ፔንስልቬንያ የሞት ቅጣትን የሻረች የመጀመሪያው ግዛት ናት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሌሎች በርካታ ግዛቶች ውስጥ የሞት ቅጣት ተከልክሏል፡፡
4. ስለሞት ቅጣት የሚነሱ ክርክሮች እና ቅጣቱ የሚጣልበት ወንጀል አይነት
የሞት ቅጣት በተለየ ሁኔታ ከባድ ተብለው የተደነገጉ ወንጀሎችን ፈጽመዉ በተገኙ ወንጀለኞች ላይ ሕይዎታቸዉን አንዲያጡ የሚፈረድ ፍርድ ነዉ፡፡ የሞት ቅጣት ክቡር የሆነዉን የሰውን ህይወት የሚያሳጣ የቅጣት አይነት በመሆኑ ሁለት ተቃራኒ አቋሞች ያሉትና በብዙ መንግስታት እና በአለም ዙሪያ ያሉ ሀገራት አከራካሪ ጉዳይ ነዉ።
ከሞት ቅጣት ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ የመጀመርያዉ ሀሳብ በብዛት ከሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪዎች አንጻር የሚነሳ ሲሆን እሱም የመኖር መብት የሠው ልጆች በተፈጥሮ የተጎናጸፉት መብት በመሆኑ ምንም እንኳን ሰዎች ከባድ ወንጀል ቢፈጽሙ ይህንን መብታቸውን በተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ሰው እጅ ሊያጡ የማይገባ ነው የሚል መከራከርያ ነው፡፡ በተቃራኒዉ የሚነሳዉ ሁለተኛዉ ሀሳብ ደግሞ የመኖር መብት የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የተገኘ መብት ቢሆንም ከባባድ ለሆኑ ወንጀሎች የሞት ቅጣትን መጣል ሌሎችን ለማስተማር እና ወንጀል እንዳይፈጸም ለመከላከል በልዩ ሁኔታ የመኖር መብት ላይ ገደብ ሊጣልበት ይገባል የሚል ነዉ፡፡
አብዛኛዉ አገራት ከቅርብ ግዜ ወዲህ የሞት ቅጣት አንዳይፈጸም እያገዱ ወይም ከህጋቸዉ ዉስጥ እያወጡ በመሆኑ ቅጣቱ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ እንደ ዎረልድ አትላስ (World Atlas) ሪፖርት አሁን ላይ በሞት ቅጣት የሚቀጡ አገሮች ከዓለም አገሮች አንድ ሦስተኛ ያህሉ ብቻ ሲሆኑ አገራችንን ጨምሮ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ቻይና፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ (የተወሰኑ ግዛቶች ከህጋቸዉ ዉስጥ ሰርዘዉታል)፣ አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ሱዳንን እና ሌሎችም ይገኙበታል። በአንጻሩ ደግሞ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ሁሉም የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት የሞት ቅጣትን ከህጋቸዉ ዉስጥ ሰርዘዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የሞት ቅጣትን በሚፈጽሙ አገሮች ውስጥ ቅጣቱ ለከባድ ወንጀሎች ላይ የሚጣል ሲሆን ከእነዚህ ወንጀሎች መካከል ግድያ፣ ሽብርተኝነት፣ አስገድዶ መድፈር፣ አፈና እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገወጥ ዕፅ ዝዉዉር እና ሙስና ናቸዉ፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ የአረብ አገሮች እንደ ሴተኛ አዳሪነት፣ ግብረ ሰዶም እና ዝሙት ያሉ አንዳንድ የወሲብ ወንጀሎች በሞት ቅጣት ያስቀጣሉ።
በሞት ቅጣት ላይ ያለዉ ልዩነት አንዳለ ሆኖ በጊዜ ሂደት አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚከተሉትን ጨምሮ የሞት ቅጣትን የሚከለክሉ በርካታ አለማቀፍ ሰምምነቶችን አዉትቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡
• አለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ የሞት ቅጣትን ለማስወገድ ታልሞ የወጣዉ ሁለተኛው አማራጭ ፕሮቶኮል (The Second Optional Protocol to the International Covenant on Civil and Political Rights)፡፡
• የሞት ቅጣትን ስለማስወገድ ለአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት ፕሮቶኮል ቁጥር 6 እና ለአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት ፕሮቶኮል ቁጥር 13 በሁሉም ሁኔታዎች የሞት ቅጣትን ለመሰረዝ የወጡ (Protocol No. 6 to the European Convention on Human Rights, and Protocol No. 13 to the European Convention on Human Rights)።
• የሞት ቅጣትን ለማስወገድ የአሜሪካ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት ፕሮቶኮል (The Protocol to the American Convention on Human Rights to Abolish the Death Penalty)።
5. የሞት ቅጣት አፈጻጸም አይነቶች
የሞት ቅጣት የአፈፃፀም ዘዴዉ በብዛት በህግ የሚወሰን ይሆናል፡፡ የሚተገበረዉ የሞት ቅጣት በወንጀል አድራጊው ላይ አላስፈላጊ ስቃይና እንግልት ማምጣት የለበትም። አሁን ላይ በተለያዩ አገራት ከሚተገበሩት የአፈፃፀም ዓይነቶች መካከል የኤሌክትሪክ ወንበር ወይም ኤሌክትሮይክ፣ ገዳይ መርፌዎች፣ መታነቅ፣ አንገት መቁረጥ እና በተኩስ መገደል ይገኙበታል።
6. የሞት ቅጣት በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን በወንጀል ህጓ ዉስጥ እዉቅና በመስጠት ተግባራዊ እያደረገች ያለች ሀገር ናት፡፡ በወንጀል ህጋችን ዉስጥ የሞት ቅጣት በተለዬ ሁኔታ ከባድ ተብለው ለሚገመቱ ወንጀሎች የሚደነገግ የቅጣት ዓይነት ነው፡፡
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 117(1) መሰረት የሞት ቅጣት በአጥፊዎች/ጥፋተኛ በተባሉ ሰዎች ላይ የሚፈረደው የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ከግምት ውስጥ ገብተው ነው፡፡ እነኚህም፡-
1. የወንጀል ድርጊቱ በሞት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ወንጀሉን በሚያቋቋመው የህጉ ልዩ ክፍል በግልጽ ተደንግጎ ሲገኝ፣
2. ወንጀሉ ፍፃሜ ያገኘ ማለትም በሙከራ ደረጃ ላይ ያልተገታ ሲሆን፣
3. ቅጣቱን የሚያቀልለት ምንም አይነት ማቅለያ ምክንያት የሌለ እንደሆነ፣
4. የተፈፀመው ወንጀል እጅግ በጣም ከባድና ወንጀለኛው በተለይ አደገኛ ሲሆን እና
5. አጥፊው የቅጣት ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ እድሜው 18 የሞላዉ ከሆነ ነዉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት መስፈርቶች በተጨማሪ የተላለፈዉ የሞት ቅጣት ለመጽናትና ተፈጻሚ ለመሆን የአገሪቱን ርዕሰብሔር ፈቃድ አስፈላጊ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን በህግ የሞት ቅጣት ያለ ቢሆንም በርዕሰብሄሩ መፅናት የሚገባው በመሆኑ እና በሌሌች እንደ ይቅርታና ምህረት ምክንያቶች በአገራችን ተፈፃሚነቱ ዝቅተኛ ነዉ፡፡
በሌላ በኩል አፈጻጸሙን ስንመለከት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች ፍርዱ በህዝብ ፊት በአደባባይ፣ በስቅላት ወይም በማንኛውም ኢ-ሰብዓዊ መንገድ ሊፈጸምባቸው እንደማይገባ በአንቀጽ 117(3) ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ቅጣቱ የሚፈጸመዉ የሚመለከተዉ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የበላይ ሃላፊ በሚወስነዉ የአፈጻጸም ዘዴ/ሁኔታ በማረሚ ቤቱ ቅጥር ጊቢ ዉስጥ ይሆናል፡፡ የሞት ቅጣቱ ከመፈጸሙ በፊት በተቀጪዉ ላይ ምንም አይነት የበቀል እረምጃ፣ የአካል ጉዳትና ስቃይ ማድረስ በፍጹም የተከለከለ ነዉ፡፡
7. የሞት ቅጣት ታግዶ የሚቆይበት ሁኔታ (አንቀጽ 119)
ነብሰ ጡር ሴቶች እና ኢ-ሀላፊ እና ከፊል የወንጀል ሀላፊነት ላይ የሚገኙ እና የታመሙ ሰዎች ምንም እንኳን የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ቢሆንም ከዚሁ ሁኔታ ውስጥ ወጥተው እስኪገኙ ድረስ የሞት ፍርዱ ሳይፈጸም ተንጠልጥሎ ይቆያል፡፡ ነብሰ ጡሯ ፍርደኛ በሰላም ከተገላገለች እና ህጻኑን ማሳደግ እንዳለባት ፍ/ቤቱ ሲያምን የሞት ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊለውጥላት ይችላል፡፡
ከዚህ ሌላ ይህ አይነቱ ቅጣት በምህረት ወይም በይቅርታ ሊለወጥ ወይም ቀሪ ሊሆን እንሚችል የወንጀል ህጉ በአንቀጽ 120 (1 እና 2) ስር በግልጽ ይደነግጋል፡፡
8. የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሰዉ ቅጣቱ እስኪፈጸም የሚቆይበት ሁኔታ
የሞት ቅጣት የተፈረደበት ሰዉ ቅጣቱ እስኪጸናና እስኪፈጸም ድረስ ጽኑ እስራት የተፈረደበት እስረኛ እስራቱን በሚፈጽምበት ሁኔታ የማረሚያ ቤት አስተዳደር አስፈላጊዉን የደህንነት ጥበቃ እያደረገለት ታስሮ የሚቆይ ይሆናል፡፡
Source:- Ministry of Justice