13/10/2022
በህይወት የሌሉና በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በባንክ ያላቸውን ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀስ የቆየ ሂሳብ ደንበኞቹ እንዳሉና እንደቀረቡ አስመስለው በማንቀሳቀስ ገንዘቡን ለሌሎች ሰዎች በማስተላለፍ በድምሩ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ሰባት የአዋሽ ባንክ ሰራተኞች ላይ ዐቃቤ ህግ ክስ መሰረተ፡፡
ተከሳሾቹ 1ኛ አቶ ሐብታሙ ደረሰ ጅማ (በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበረ)
2ኛ አቶ ወርቁ ኃይሉ ጫሊ ( በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ የነበረ)
3ኛ አቶ ፈጠነ ገ/እግዚአብሔር ነጋ (በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች ግንኙነት መኮንን የነበረ)
4ኛ አቶ ደበላ ንጉሴ ወርቅነህ ( በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበረ)
5ኛ አቶ ምስጋናው ያረጋል አንለይ ( በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበረ )
6ኛ አቶ ሮባ ታደለ ዲንቃ ( በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ ሂሳብ ሹም የነበረ)
7ኛ ተከሳሽ ጉግሳ ( በአዋሽ ባንክ የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበረ)
ሲሆኑ የተሰጣቸዉ ሥልጣን እና ኃላፊነት አላግባብ በመገልገል በህይወት የሌሉ ደንበኞችን ጨምሮ የሂሳብ ባለቤቶቹ ሳይቀርቡ እንደቀረቡ በማስመሰል እና ሂሳቡን ተንቀሳቃሽ (Active) በማድረግ አጠቃላይ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወስደዋል በሚል ዐቃቤ ህግ 4 ተደራራቢ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው ተከሳሾቹ
1ኛ ወ/ሮ ብርሃን ዳባ በተባለች የባንኩ ደንበኛ ለረዥም ጊዜ ያልተንቀሳቀሰ ገንዘብ ደንበኛዋ በህይወት ሳትኖር ቀርባ ሂሳቡን ያንቀሳቀሰች በማስመሰል እ.ኤ.አ ከ23/10/20 እስከ 30/10/2020 ዓ.ም ባሉት 7 ቀናት ውስጥ በ3 የሂሳብ ዝውውሮች የሂሳብ እንቅስቃሴውን በመቀበል እና በማጽደቅ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ከማይንቀሳቀስ ሂሳብ 10,000 (አስር ሺ) ብር በማስተላለፍ ሂሳቡ ተንቀሳቃሽ (Active) እንዲሆን እና ሌሎች የሂሳብ ዝውውሮች እንዲፈፀሙ በማድረግ 1,603,000 (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሦስት ሺ) ብር፤ 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ 1,593,000 (አንድ ሚሊየን አምስት መቶ ዘጠና ሦስት ሺ) ብር እንዲሁም 6ኛ ተከሳሽ 795,000 (ሰባት መቶ ጠና አምስት ሺ) ብር ከወ/ሮ ብርሃን ዳባ ሂሳብ ተቀናሽ አድርገው ወደ ሌላ ቅርንጫፍ እና ባንክ በማስተላለፍ ዝውውር እንዲፈፀም በማድረግ ፣
2ኛ በውጪ ሃገር በምትኖረው ወ/ሮአስናቁ ተሾመ ገ/ማርያም በተባለች ደንበኛ ለረዥም ጊዜ ያልተንቀሳቀሰ ሂሳብ ደንበኛዋ ቀርባ ሂሳቡን ያንቀሳቀሰች በማስመሰል 1ኛ፣ 2ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ከማይንቀሳቀስ ሂሳብ 10,000 (አስር ሺ) ብር በማስተላለፍ ሂሳቡ ተንቀሳቃሽ (Active) እንዲሆን በማድረግ እ.ኤ.አ በ11/11/20 እና በ12/11/2020 ዓም በ2 ቀናት በተካሄዱ 2 የሂሳብ ዝውውሮች ከወ/ሮአስናቁ ተሾመ ሂሳብ አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሁለት ሺህ (1,402,000) ብር ተቀናሽ በማድረግ የሂሳብ ዝውውር እንዲፈፀም በማድረጋቸው፣
3ኛ ኦመር መሀመድ ደዋም የተባለ ደንበኛ በተንቀሳቃሽ ሂሳብ የሚገኝን ለረዥም ጊዜ ያልተንቀሳቀሰ ገንዘብ ደንበኛው ሳይቀርብ ቀርቦ ሂሳቡን ያንቀሳቀሰ በማስመሰል እ.ኤ.አ 10/09/20 (5/13/12ዓም) በተዘጋጀ ሐሰተኛ የሐዋላ መላኪያ ቅጽ በመጠቀም ከኦመር መሀመድ ሂሳብ ተቀናሽ አድርገው ወደ ሌላ ቅርንጫፍ በማስተላለፍ 191,000 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሺ) ብር ዝውውር እንዲፈፀም በማድረግ እና
4ኛ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት በወ/ሮ አስቴር ምህረቱ ስም በተከፈተ የቁጠባ ሂሳብ የሚገኝን ለረዥም ጊዜ ያልተንቀሳቀሰ ገንዘብ ደንበኛዋ ቀርባ ሂሳቡን ያንቀሳቀሰች በማስመሰል ከእ.ኤ.አ 24/11/20 እስከ 07/12/20 ዓም ባሉት አጭር ቀናት በተካሄዱ 3 የሂሳብ ዝውውሮች የሂሳብ እንቅስቃሴውን በመቀበል እና በማጽደቅ 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከማይንቀሳቀስ ሂሳብ 10,000 ብር በማስተላለፍ ሂሳቡ ተንቀሳቃሽ (Active)እንዲሆን በማድረግ ከአስቴር ምህረቴ ሂሳብ 2,510,000 (ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ አስር ሺ) ተቀናሽ አድርገው ወደ ሌላ ባንክ እና ቅርንጫፍ በማስተላለፍ የባንኩ ንብረት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረጉ በመሆኑ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1) (ሀ)፣ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ (9)(2) ላይ የተደነገገውን መተላለፍ በፈፀሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል በ4 ተደራራቢ ክሶች ተከሰዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ክስ ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን ክሱን ለማንበብ ለጥቅምት 8/2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡