10/05/2026
የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በገራዶ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የ110 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ
ደሴ (ግንቦት 02/2018 ዓ.ም)
የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ድርሻውን ለመወጣት በገራዶ አካባቢ ለሚገኙ ተፈናቃዮችና ወላጅ አልባ ሕፃናት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
ኮሌጁ ሚያዚያ 28 እና 29 ቀን 2018 ዓ.ም ባከናወነው በዚህ የድጋፍ መርሃ-ግብር ላይ ከ110 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የምግብ ፍጆታዎችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን አበርክቷል።
ድጋፉን ያስረከቡት የኮሌጁ የአካዳሚክ ም/ዲን ወ/ሮ መምበረ ላቀው እና የልማትና አስተዳደር ም/ዲን አቶ ደምሰው አሰፋ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና ለተቸገሩ ወገኖች አለኝታነቱን ለማሳየት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
የቀረበው ድጋፍም ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ ሶፍት እና ኦሞን ያካተተ ሲሆን፤ ይህም በተፈናቃዮችና በሕጻናቱ ላይ የሚታየውን መሰረታዊ ፍላጎት በከፊል ለመሸፈን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ አሸብር ወሰንና የኮሌጁ አመራሮች ተገኝተው ድጋፉን ለተወካዮች አስረክበዋል። እርዳታውን የተቀበሉት ግለሰቦች ኮሌጁ ላደረገላቸው ወቅታዊና አስፈላጊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መሰል ሰብአዊ ድጋፎችንና የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።