12/04/2026
ከሆሳዕና እስከ ኢየሩሳሌም ከኢየሩሳሌም እስከ ጎልጎታ፡ ዝንፍ ያላለው መለኮታዊ የክርሰቶስ ተልእኮ
፬፬፬፬፬፬፬፬፬፬፬፬፭፬፭፬፬፬፬፬፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭፭
በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ጉዞ ፍጻሜውን ያገኘበት "የሕመም ሳምንት" (ሰሙነ ሕመማት) የሰው ልጅ ታሪክ የተቀየረበት የታላቅ ተልእኮ ምዕራፍ ነው። ይህ ጉዞ በሥጋዊ መለኪያ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችንና ጥቂት ሰዓታትን የፈጀ ቢመስልም፣ በመንፈሳዊ መለኪያ ግን ከአዳም ውድቀት እስከ ዳግም ምጽዓት ያለውን የሰው ልጅ ዕዳ የዘጋበት መለኮታዊ ጉዞ ነው።
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በክብር ከገባበት (ሆሳዕና) አንስቶ በጎልጎታ ሕይወቱን አሳልፎ እስከሰጠበት (ዓርብ) ድረስ ያለው ጊዜ 120 ሰዓታት (አምስት ቀናት) ገደማ ነው። እያንዳንዱ ሰከንድ፣ እያንዳንዱ እርምጃ፣ እያንዳንዱ የሆታና የግርፋት ድምፅ በነቢያት የተነገረውን The Divine Timetable "መለኮታዊ የጊዜ ሰሌዳ" ጠብቆ የተከናወነ ነበር። ይህም ጌታችን በታሪክ ማዕበል ውስጥ ዝም ብሎ የተነዳ ሳይሆን፣ ዓለምን የማዳን ዓላማውን ዝንፍ ሳይል እየመራ እንደነበረ ያሳየናል።
ኢየሩሳሌም የንጉሡ ከተማ ናት፤ ጎልጎታ ደግሞ የሞት ስፍራ ናት። ጌታችን ከከተማው ክብር ወጥቶ ወደ ቆሻሻውና ወደ ተናቀው የራስ ቅል ስፍራ (ጎልጎታ) መጓዙ፣ የሰውን ልጅ ከውርደት ወደ ክብር ለማውጣት የከፈለው መለኮታዊ ልውውጥ ነው። በመንገዱ ላይ ሁለት ተቃራኒ አቀባበሎች ገጥመውታል፦
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የነበረው አቀባበል በእልልታ፣ በሆታ እና "የክብር ንጉሥ ሆይ፤ አሁን ናና አድን! ሀሆሳእና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሳእና በዓርያም" በሚሉ የሆሳዕና ድምጾች የታጀበ ነበር። ይህ አቀባበል በሰውኛ እይታ ሲታይ፣ የድልና የክብር ሰካር ውስጥ በመቅረት ቀጣዩን ምዕራፍ—ማለትም ስድብ፣ ግርፋትና ሽሙጥ የሞላበትን የመስቀል ጎዳና—ለመሸሽ የሚያስገድድ "አማላይ ፈተና" ሊሆን ይችል ነበር።
በእርግጥም የሆሳዕናው ዝማሬና "ንጉሥ ነህ፣ አዳኝ ነህ" የሚሉት ድምጾች ለእርሱ የተገቡና እውነተኛ ነበሩ። እነዚህን ቃላት "የሐሰት ውዳሴ አይደሉም" የምንልባቸው ሦስት ዓበይት ምክንያቶች አሉ፦
1. የትንቢት ቃል ፍጻሜ መሆኑ፦ ነቢያት ቀድመው የተናገሩት ቃል በዝርዝር የተፈጸመበት በመሆኑ።
2. እያንዳንዱ የምስጋና ቃል ለባሕርይ አምላክነቱና ለክብሩ የሚመጥን በመሆኑ።
3. ጌታ ምስጋናውን በጸጋ መቀበሉና ትክክለኛነቱን ማረጋገጡ።
የካህናት አለቆችና ጻፎች ቅናት አድሮባቸው "ዝም አሰኛቸው" ባሉት ጊዜ፣ ጌታ የሰጠው ምላሽ "እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ።" ይህ የሚያሳየው ፍጥረት ሁሉ ለፈጣሪው ምስጋና ማቅረብ ተፈጥሯዊ ግዴታው መሆኑን ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የዕለቱ ውዳሴ "ከንቱና ግብዝ" ነበር ሊባል የሚችልባቸው አሳማኝ ምክንያቶች አሉ። ይህም የሕዝቡ የትንቢት አረዳድ ከተንሸዋረረ አመለካከት የመነጨ በመሆኑ ነው። እርሱ የዋህ ንጉሥ ሆኖ ሊያድን ሲመጣ፣ ሕዝቡ ግን ንግሥናውንና አዳኝነቱን የተረዱበት መንገድ ፍጹም ለየቅል ነበር።
ጌታ ግን በተደረገለት ደማቅ አቀባበል ተመስጦና ተደምሞ ወንበዴዎችን ከመቅደሱ ጠርጎ ከማውጣት ወደ ኋላ አላለም። ይህም ክብሩ ከሰው ምስጋና ሳይሆን ከቅድስናው እንደሚመነጭ ማሳያ ነው። ጌታ አዳኝነቱን ሊገልጽ የፈለገው በዘንባባ ዝንጣፊ፣ በሆታና በእልልታ "አሸሼ ገዳሜ" በማለት ሳይሆን፤ የእሾህ አክሊል ደፍቶ፣ በጎልጎታ ኮረብታ ላይ፣ በጣር ድምፅ "ተፈጸመ" በሚል ታላቅ ድል ነበር።
የሰው ልጅ ተለዋዋጭነት የሚገለጠው እዚህ ላይ ነው፦
• በኃጢአተኞች ክንድ ሲያዝ፣ ገላው በጅራፍ ሲተለተል፣ በኢየሩሳሌም አደባባይ የድል ምልክት የነበሩት ዘንባባዎች ረገፉ።
• በዘንባባው ፋንታ የእሾህ አክሊል ሲደፋ፣ የሕመም ምልክት የሆነውን መስቀል ሲሸከም እና እጆቹ በችንካር ሲቸነከሩ፣ ያ "ሆሳዕና" የሚለው ድምፅ ወደ "ድንቄም አዳኝ" ሽሙጥ ተቀየረ።
በሳምንት ጊዜ ውስጥ ምንጣፉን የሚያነጥፍለት የነበረው ያ መንጋ፣ ራሱን ከሮማውያን ቀንበር የሚያላቅቅ ምድራዊ ፖለቲከኛ ፈላጊ ነበር። ጥቅሙ ሲነካና የጠበቀው ምድራዊ ድል ሲዘገይ፣ ሳይታክት "ሆሳዕና" ይል የነበረው አንደበት "ይሰቀል! ይሰቀል!" ወደሚል ጩኸት ተለወጠ። "በርባንን ፍታልን" በማለትም የወንበዴ ወዳጅ ለመሆን አላፈረም።
ነገር ግን ክርስቶስ በሰው ድጋፍ አልነገሠም፣ በሰው ተቃውሞም ከዙፋኑ አልወረደም። ሲያነግሱት ንጉሥ ነበር፣ ሲሰቅሉትም ያው ንጉሥ ነው። የእርሱ ዓላማ በሰው ውዳሴ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ በሰማያዊው የአባቱ ፈቃድ ላይ የቆመ ስለነበረ።የወደቀባቸው ጎዳናዎች ሁሉ የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት የወደቀበትን ጥልቅ ጉድጓድ የሚደፍኑ ነበሩ።"እርሱ በሥጋ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።" (ፊልጵስዩስ 2:8) ክርስቶስ እውነተኛውን የድል አክሊል የተቀዳጀው በዘንባባው አቀባበል ሳይሆን በመስቀሉ መሥዋዕትነት ነው።
ሕይወት ሁልጊዜ የዝንባባ ዝማሬና የ"ሆሳዕና" እልልታ ብቻ አይደለችም። ከክብር መግቢያው ጀርባ የጎልጎታ አቀበት፣ የግርፋት ድምፅና የችንካር ሕመም አለ።
እውነተኛው ፈውስና ትንሳኤ የሚገኘው በመስቀሉ መንገድ፣ በስቃይና በይቅርታ ውስጥ ነው። ለጠላት "ሞት" የሚመስለው የመስቀል መንገድ፣ ለእኛ ግን የእግዚአብሔር የድነት በር ነው።
"ተፈጸመ" ሲል፣ ሰዓቱ መቆሙን ሳይሆን፣ የተሰጠው መለኮታዊ ተልእኮ አብ የጠየቀው የጽድቅ ጥያቄ የሰውልጅ የዘመናት የሀጢያት እዳ ምንም ሳይቀረው ተከፍሎ በድል መጠናቀቁን ማብሰሩ ነበር።
ዛሬም ጥያቄው፦ "ጌታ እንዴት እንዲያድነን ነው የምንጠብቀው?"
ዛሬ እኛ እግዚአብሔርን እንዴት እንዲፈውሰንና እንዴት እንዲያድነን ነው የምንጠብቀው? "አዳኝ ነው" ብለን ዘምረን፣ እርሱ ግን እንዴት እንደሚያድን ካላወቅን ታላቅ ስህተት ላይ ነን። እውነተኛው ድኅነት ከመስቀሉ መንገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
መስቀሉ የግል ሕይወታችንን ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም እይታችንን (Worldview)፣ ርዕዮተ-ዓለማችንንና ፖለቲካችንን ጭምር የሚፈውስ ኃይል ነው። ዛሬ በሀገራችን ላለው መባላት፣ መነካከስና እልቂት እውነተኛ ፈውስ የምናገኘው በዚሁ በመስቀሉ መንገድ በትሕትና፣ ራስን በመስጠትና በይቅርታ መንገድ ብቻ ነው።
መስቀሉ ወደ ትንሣኤ ክብርና ወደ ብርሃኑ ዓለም መሸጋገሪያ ድልድያችን ነው። እርሱ መድኃኒታችን፣ ኃይላችንና ሰላማችን ነውና። መልካም አውድዓመት!!