07/07/2023
የስም ሀብታም ነኝ። ማለቴ ብዙ መጠሪያ ስም ነው ያለኝ። ከ’ነሱ ውስጥ አንዱ ዛህራ ነው። ይህንን ስም ያወጡልኝ የቁርዓን ቤት ሸኼ ናቸው። ይወዱኝ ነበር። ለዛም ይሆናል ስም ያወጡልኝ። እሳቸው ከሌሉ በቦታቸው ይሾሙኛል። እናም እርሳቸውና የቁርዓን ቤት ልጆች በዚህ ስም ነው የሚጠሩኝ። ትዝ ይለኛል። እንደዛሬው ጁምዓ ሲሆን ቂርዓት አይኖርም ነበር። የእረፍት ቀን ነው። ቁርዓን ከምንቀራባት ትንሿ መስጊድ በቅርበት የምንኖር ልጆች በጠዋት ሄደን የሸኻችንን ጀለብያና ጥምጣም እናጥብላቸዋለን። ልብሳቸው እስኪደርቅ ፀሐይ እየሞቁ፣ ሲዋክና ሙስበሐቸውን ይዘው ጎርደድ እያሉ ይጠባበቁና ሰዓት ሲደርስ ለባብሰው ወደ ዋናው መስጅድ ይሄዳሉ።
ሸኻችን እንደዬአቅማችን ያስቀሩንና "በሉ ሀይያ ከርሩ!" ይሉናል። ያስቀሩንን በትእዛዛቸው መሰረት ደጋግመን እናጠናና "ተሰሙን" ብለን ዞረን እርሳቸው ጋር እንቀርባለን። ያኔ እንደ አሁኑ የቁርዓኑን ምዕራፎች በስም አናውቃቸውም ነበር። በምዕራፎቹ መጀመሪያ ላይ በሚገኘው አንቀፅ ቃል እንጂ። "የት ደረስሽ?" "ፈሰብቢህ!" ማን ጋር ነሽ? "ተባረክን አለፍኩ።" በአንዳንድ ምዕራፎች መጨረሻ ላይ ካለው ቃል ጋር ደግሞ አዛምደን እንገጥም ነበር። ለምሳሌ በሱረቱል ፈትሕ መጨረሻ ላይ ኢንነሁ ካነ ተውዋባ ካልን በኋላ የሸኻችን ላም ትንቧቧ እንል ነበር። ሱረቱዱሐ ላይ ደግሞ ወአምማ ቢኒዕመቲ ረብቢከ ፈሐድዲስ ብለን የሸኻችን ልብስ ሁሉም አዳዲስ እንላለን። ሌላው በሌሎች አካባቢዎች ሲቀራ አናባቢ ምልክቶች ፈትሐ፣ ከስራ፣ ዾማ እንደሚባሉት ደሴ ነስባ፣ ኪፍዻ፣ ኡርፋ ነበር የምንለው። የአሊፉን ነስባ አ…ኪፍዻውን ኢ…ኡርፋውን ኡ አ ኢ ኡ። የቁርዓኑን ቃላት አቀጣጥሎ የመቅራት ስልት "ሸድዳ" የሚባል ሲሆን (ከማጥበቂያው ሸድዳ የተለዬ ነው) ጀማሪዎች የሚጠቀሙት ፊደላቱን ነጣጥሎ ቀርቶ በመጨረሻ ማገጣጠም "ውጥጥ" ይባላል። ሌላው ነገር አድጌ ትርጉሙን ከተረዳሁ በኋላ እንደገመትኩት ምናልባት በልጅነት አንደበት የትርጉም መፋለስ እንዳያመጣ ከመስጋት ይመስለኛል ሸኾቻችን ሱረቱል ካፊሩንን ያዘልሉን ነበር። ሙስሊም ያልሆኑ ወዳጆቻችን ታድያ እንደ ከባድ ግኝት "ቁርዓን ውስጥ ሳይቀራ የሚታለፍ ሚስጥር አለ!" እያሉ ይንሾካሾኩ ነበር።😆
ከሁሉም ደስ የሚለው በዬደረጃው ደግሰን የምናበላው ነገር ነው። ከላይ ወደታች ስለነበረ የምንቀራው ኢቅራዕ ላይ የደረሰ ቆሎ ያበላል። ዐምመን የጨረሰ ድፎ ያስደፋና ከጆሊጁስ ጋር ያመጣል። እንዲህ እንዲህ እያለ ጊዜው ደርሶ ሲኸተምማ ደስታ ነው። ሰደቃ ነው። በግ ይታረዳ
ል።
እንዲህ እ
ንደዛሬው እንደ አጭር ኮርስ የሶስት ወር ለብ ለብ ሳይሆን በፊት የቁርዓን ኺታም ይሄን የመሰለ ወዝና ለዛ ነበረው።
My ቂርኣት style via atiqa ahmed ali
ጁምዓ ሙባረክ!💚💚💚