18/10/2019
ወዳጄ ሆይ
ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ኀዘን የልብ መሰበርን ያመጣል፣ የልብ መሰበርም እግዚአብሔርን ያያል። መገፍተር ሲያቅትህ ያቀፍከው የወደድከው አይደለም። አገርን የትኛውም ጠላት ማፍረስ አይችልም፣ አገርን የሚያፈርሱት የአገሬው ሰዎች ናቸው። እንኳን ጠላት ያለበት ወዳጅ ያለውም የሚጠቃው በመጠጥ ነው። መልካም ባልንጀራ መፈለግ ያደክማል፣ መሆን ግን ያሳርፋል። ለምኖ አነሰ ማለትና መሳደብ ታላቅ ውርደት ነው። እጅህ የሚሠራልህን የሰው እጅ አይሠራልህምና ሌሎች ይሥሩልኝ ብለህ አትቀመጥ። እንደ ደረስህ በር አትግፋ፣ አንኳኳ። እንደ ሰማህም ቱግ አትበል ፣ አጣራ። ተበደልሁ እንጂ በደልሁ የሚል እየጠፋ ነው። ሰላም ራሳቸውን ባጸደቁ ሳይሆን ንስሐ በሚገቡ ትሑታን ጋ ትኖራለች። ሙትን ሲያወግዙ መኖር ተናጋሪ ሙት መሆን ነው። ዘረኝነት በቃል የተወገዘ በተግባር የሚኖሩት አስመሳይነት ነው። የጋራ ጠላት ከሌለው የጋራ ፍቅር የሚያጣ ሕዝብ ምስኪን ነው።
ወዳጄ ሆይ
ሁሉን ነገር ለእኔ የሚሉ ሕፃናት፣ ያልሰለጠኑ፣ ወፈፌና አውቆ አበዶች ናቸው። አስበው የማይናገሩ ፣ ተናግረው ያስባሉ። በሰማበት ሁሉ ጣዱኝ የሚሉ የሰፈር ምጣድ ናቸው፣ ባለቤት የላቸውም። ካህን ፖለቲካ ፖለቲካ ከሸተተ፣ ፖለቲከኛ ዕጣን፣ ዕጣን ከሸተተ ነገር ተበላሸ! ብዙ የሚያሳይ ዕድሜ፣ ልጅና እጦት ነው። በርግጥ የታመምከው እህል እምቢ ያለህ ቀን ነው፣ በርግጥ የተፈተንከው ቃለ እግዚአብሔር ያስጠላህ ቀን ነው።
ወዳጄ ሆይ
ከአዲስ ንጉሥ የቆየ ወታደር፣ ከአዲስ ባለትዳር የቆየች ሠራተኛ፣ ከአዲስ ሐኪም የቆየ በሽተኛ፣ ከአዲስ ባለጠጋ የቆየ ደላላ፣ ከአዲስ ሰባኪ የቆየ የደብር ዘበኛ፣ ከአዲስ መካሪ የቆየ ጥፋተኛ፣ ከአዲስ ቄስ የቆየች አቃቢት ይበልጣሉ። የከረመ ወይን ዋጋው ትልቅ ነው፣ የበሰለም ሰው ተፈላጊ ነው። አገር የምታብደው እውነተኛ አዋቂዎቿን የናቀች ቀን ነው።