10/09/2026
መልካም አዲስ ዓመት (፳፻፲፱ ዓ.ም)!
🌻 እንቁጣጣሽ 🌻
«እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገረን!»
«እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፤ መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፤ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ»
ለመላው የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ፣ አጋሮቻችን እና ወዳጆቻችን እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
አዲሱ ዓመት ፳፻፲፱ ዓ.ም የደስታ፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የበረከት፣ የአንድነትና የስኬት ዓመት እንዲሆንልን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራር መልካም ምኞቱን ያስተላልፋል። ፈጣሪ ለሀገራችን ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ሰጥቶ ክፉውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ በማስወገድ የሰላም ዘመን ያድርግልን!
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ-ገዝነት በሚያደርገው የሽግግር ጉዞ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በአዲሱ ዓመት ሙሉ የራስ-ገዝነት እውቅናውን በመቀበል፣ በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት የመጀመሪያው ትውልድ ራስ-ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲነቱን አረጋግጦ ለመቀጠል በታላቅ ዝግጅት ላይ ይገኛል።
ይህ ወሳኝ የሽግግርና የስኬት ምዕራፍ እውን እንዲሆን ከጎናችን ለቆማችሁ፦
🌻 ለሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶቻችን፣
🌻 ለክቡራን ፕሮፌሰሮቻችን፣ መምህራኖቻችንና ተመራማሪዎቻችን፣
🌻 ለመላው የዩኒቨርሲቲያችን አስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣
🌻 በዓለም ዙሪያ የምትገኙ የቀድሞ ተማሪዎቻችንና ባለድርሻ አካላት፣
🌻 ለዓባይና ጣና ፈርጥ ለሆነችው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ማህበረሰብና አመራሮች፣
🌻 ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመስተዳድር አካላት፣
እንኳን ለ፳፻፲፱ ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማህበረሰብ በጎ ለውጥ የሚተጋ፣ የዕውቀትና የክህሎት ማዕከል በመሆን ጥበብን ለሚሹ ሁሉ ተደራሽ የሚያደርግ ተቋም ነው። ከአማራ ክልል የተለያዩ የመስተዳድር ዘርፎችና ማህበረሰብ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሕዝባችን ልማትና ልህቀት በትጋት መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።
ውድ በመላው ዓለም የምትገኙ አጋሮቻችን፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን!
ዩኒቨርሲቲያችን አሁን ከደረሰበት የልህቀት፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተልዕኮ ባሻገር በላቀ አቅምና ጉልበት ወደፊት ይገሰግስ ዘንድ በአጋርነትና በባለቤትነት አብራችሁን እንድትሠሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
መልካም አዲስ ዓመት!
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ!
www.bdu.edu.et