05/05/2026
ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.
85ኛውን የአርበኞች ድል በዓል አስመልክቶ ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የተሰጠ መግለጫ
ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን ፋሽስታዊ አገዛዝ ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላ በተመሳሳይ ቀን ተሸንፎ የወጣበት ዕለት በመሆኑ በሀገራችን የነፃነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ዕለት ነው።
ይህ እለት ፋሽዝም የተሸነፈበት ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ቀን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ ቀንም ነው። የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ለመላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለአርበኞች ቀን አደረሳችሁ ይላል።
የብልፅግና አገዛዝ የሀገሩን የፖሊሲ ሉዓላዊነት ከማከራዬት አልፎ አዬር ኃይሉን እና መሰል ተቋማትን ለውጭ ኃይሎች መፈንጫ በማድረግ በአርበኞች መስዋዕትነት የተገኘውን የሀገር ነፃነት ለርካሽ ስልጣን ሲል አሳልፎ በመስጠቱ ሀገራችን ያልተነገረ ቅኝ ግዛት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
የብልፅግና አረመኔ አገዛዝ በአምስቱ የአርበኝነት ዘመን ጣሊያን ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፈፀመው ግብ በብዙ እጥፍ የራቁ የዘር ማጥፋት እና ሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በአማራ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ነው።
የአባቶቹን ታሪክ የወረሰው ሰራዊታችን የአማራን ህዝብ ህልዉና ለማስከበር እና የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ከዘመኑ ጥቁር ፋሽስቶች ጋር በመተናነቅ ላይ ይገኛል።
ዘር አጥፊዉን አገዛዝ ታግለን በማሸነፍ የተነጠቅነዉን ሀገር ማስመለስ ግባችን እንደመሆኑ መጠን ንቅናቄው አሁን ላይ እያደረገ ያለው ትግል የቀድሞ አርበኞች ካደረጉት የነፃነት ተጋድሎ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።
ፅናትን፣ አይበገሬነትን፣ ቁርጠኝነትን በሚጠይቀው ተጋድሎ ውስጥ በመስዋዕትነት ድል እያስመዘገበ ያለው ሰራዊታችን በአማራ ህዝብ ጠላቶች ላይ የጀመረውን የህልውና ትግል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እናረጋግጣለን።
የባርነት ቀንበር የተሰበረበት የአርበኞችን ቀን ስናከብር የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህልዉና አደጋ ለማስወገድ የሚከፈለዉን ማንኛዉንም መስዋዕትነት በመክፈል ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ ቃል በመግባትም ጭምር ነው።