Woizero Siheen Polytechnic College

Woizero Siheen Polytechnic College Welcome to the Official page of Woizero Siheen Polytechnic College (Dessie). We will keep y

የወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ታሪክ

የወ/ሮ ስኂን ት/ቤት በንጉሥ ሚካኤል ልጅ በወ/ሮ ስኂን ሚካኤል በ1922 ዓ.ም ሳላይሽ በሚገኘው የልጃቸው ጃንጥራር ኃ/ማርያም አስፋው ርስት ላይ በ25,000 ብር ተሠራ፡፡ ይህም በሀገራችን ዘመናዊ የትምህርት ታሪክ ከተመሰረቱት የመጀመሪያ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ ላለፉት 89 ዓመታት በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ አልፎ አሁን ካለበት የፖሊቴክኒክነት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በሀገር አቀፍም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙዚቃው፣ በፖለቲካው እና ኢኮኖሚው ትልቅ ዝናን ያተረፉ ዜጎች የተገኙበት የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በዘመን ቅደም ተከተል የ

ቀረበው አጭር ጽሑፍ ይህንኑ ታሪክ ያሳያል፡፡

ታሪካዊ ዳራ እና እድገቱ

በ1920 ዓ.ም ወ/ሮ ስኂን ሚካኤል ከራሳቸው 25000 ማሪያ ቴሬዛ (ጠገራ ብር) እና በራሳቸው ርስት ላይ ከህልፈተ-ሕይወታቸው አስቀድመው ለልጃቸው በሰጡት ኑዛዜ መሰረት ከ2 ዓመታት በኋላ በ1922 ዓ.ም ደሴ ከተማ ሳላይሽ አካባቢ በ4 የመማሪያ ክፍሎች ተመሰረተ፤
በ1939 ዓ.ም የተማሪ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ቁጥራቸው በርከት ያሉ መማሪያ ክፍሎችን የያዘ አዲስ ሕንፃ ተገንብቶ አሁን ወዳለበት ዋናው (ስኂን) ግቢ ተዛወረ፡፡ በዚያን ወቅት ከ1ኛ - 8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምር ነበር፡፡ አሁን ዋናው ግቢ (ስኂን ግቢ) የሚገኝበት ቦታ ላይ ትምህርት ቤቱ አንዲሰራ የመሰረት ድንጋይ የጣሉት የስኂን ሚካኤል የልጅ ልጅ አልጋወራሽ መርድ አዝማች አስፋወሰን ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት 15 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተሰሩ፡፡
በ1950 ዓ.ም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከፍ አለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት የተቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥርም 63 ደርሶ ነበር፡፡
በ1953 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ለሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ለሎንዶን ጂ.ሲ.ኤ. ፈተና) እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡
በ1953 ዓ.ም እቴጌ መነን /የስኂን ሚካኤል ልጅ/ ለተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች የሚያገለግል ሕንፃ ቮኬሽናል ግቢ በ160,000 ብር አስገነቡ፡፡ በዚህ ወቅት በቀለም ትምህርት ዘርፍ ብቻ ተማሪዎችን ማስተማር በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ከቀለም ትምህርት ጐን ለጐን በመምህርነት ሙያ፣ በእርሻና ተግባረዕድ ሙያወች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ትምህርት ቤቱን በሀገሪቱ የመጀመሪያው አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሆን አድርጐታል፡፡
1956 ዓ.ም የስኂን ት/ቤት የሙዚቃ ባንድ ተቋቋመ፡፡ ባንዱ ሲቋቋም 40 ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን መምህሩም ሚ/ር ሮናልድ ቤል የተባለ አሜሪካዊ ነበር፡፡
በ1956 ዓ.ም የ1ዐኛ ክፍልን ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የ2 ዓመት የሙያ ሥልጠና በተለያዩ መስኮች በመውሰድ ዲኘሎማ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ 1976 ዓ.ም ቀጠለ፡፡
በ1972 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም የካቲት 66 አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ከዚያም የካቲት 66 የቀለም ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት በሚል ተቀይሮ፣ ከዚያም የካቲት 66 የቀለም፣ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ተባለ፡፡
በ1980 ዓ.ም በ10+3 የቴክኒክና ሙያ መርሀ-ግብር ስልጠና መስጠት ጀመረ
በ1977 ዓ.ም የ1ዐኛ ክፍል ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ለ2ኛ ደረጃ ሠርቲፍኬት ሥልጠና ጀመሩ፡፡ ይህም ሁኔታ እስከ 1980 ዓ.ም ቀጠለ፡፡ ከዚህ በኋላ የሥልጠናው ጊዜ ከ2 ዓመት ወደ 3 ዓመት ከፍ አለ፡፡
በ1984 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም ወ/ሮ ስኂን የቀለም ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ተብሎ ተሰየመ፡፡
በ1992 ዓ.ም ሲሰጡ ከነበሩት የሙያ ስልጠና ዓይነቶች በተጨማሪ የኮንስትራክሽን የሥልጠና ዘርፍ ተከፈተ፡፡
በ1993 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋም ሆነ፡፡
በ1994 ዓ.ም የት/ቤቱ ስም ወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ተቋም በሚል እንዲጠራ ተደርጐ በተለያዩ የሥልጠና ዘርፎች በመደበኛና በማታ መርሃ-ግብር የ1ዐ+1 እና 1ዐ+2 ሥልጠናዎች በመስጠት በሰርቲፍኬት ደረጃ ማስመረቅ ጀመረ፡፡
በ1996 ዓ.ም ተቋሙ ከደሴ ቴክኒክና ሙያ ተቋም ጋር ተቀላቀለ፡፡
በ1996 ዓ.ም ተቋሙ በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሴት ሠልጣኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ፡፡
የሙያ መስኮቹም 19 ደረሱ፡፡
በ2000 ዓ.ም ተቋሙ ከደሴ ቢዝነስና ሥራ አመራር ኮሌጅ ጋር ተዋህዶ ስሙም ወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ በሚል ተቀየረ፡፡
በ2003 ዓ.ም ኮሌጁ ወደ ወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አደገ፡፡ በዚሁ ዓመትም በደረጃ 5 ስልጠና መስጠት ጀመረ፤


ስልጠና የሚሰጥባቸው ግቢዎች፡-
1. ስኂን ካምፓስ (ዋናው ግቢ)፡- ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ፣ ሆቴል ባህልና ቱሪዝም፣ ከተማ ግብርና እና ከተማ አገልግሎት (Urban Agriculture& Municipality)፣ እንዲሁም የጨርቃጨርቃ እና አልባሳት (Garment &Textile) ስልጠና ዘርፎች
2. ቮኬሽናል ካምፓስ (መነን ህንጻ)፡ ብረታ ብረት ምህንድስና (Metal Manufacturing & Engineering) ዘርፍ ማሰልጠኛ
3. ሆጤ ካምፓስ፡ የኮንስትራክሽን ስልጠና ዘርፎች ማሰልጠኛና የማምረቻ ማዕከል (ማምረቻ ዩኒትን) የያዘ
4. መርሆ ካምፓስ (የቀድሞ የአልጋወራሽ ቤተ-መንግስት የነበረና በኋላም ቢዝነስ እና ስራ አመራር ኮሌጅ የተመሰረተበት)፡ አሁን የInformation & Telecommunication ስልጠና ዘርፍ የሚሰጥበት፤ እንዲሁም የመርሆ ቤተ-መንግስት የሚገኝበት
5. ዳውዶ ካምፓስ (የቀድሞው SDC ተቋም)፡- የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጅ እና የእንጨት ስራ (Furniture) ዘርፎች ማሰልጠኛ ናቸው፡፡


ኮሌጁ አሁን ያለበት ሁኔታ፡-

ከላይ እንደተገፀው ኮሌጁ በ2000 ዓ.ም ቀደም ሲል የተመሰረቱትን የወ/ሮ ስኂን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋምን፤ የደሴ ቢዝነስና ሥራ አመራር ኮሌጅን እና የደሴ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋምን በማዋሃድ የተደራጀ ሲሆን፤ ወደ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅነት ደረጃ ያደገው ደግሞ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮሌጁ ያለበትን ሁኔታ ስንመለከት

 ስልጠና የሚሰጠው ከደረጃ 1 እስከ 5 በ0 ዋና ዋና ስልጠና ዘርፎችና ከ56 በሚበልጡ ሙያዎች ሲሆን እያንዳንዱ ሰልጣኝ በየደረጃው ተመዝኖ ብቁ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት እስከ ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ድረስ ባለው ሁኔታ 5975 የሚጠጉ ሰልጣኞችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
 አዳዲስ የሙያ መስኮች ከመከፈታቸው በፊት የአካባቢውን ገበያ እና ኢንዱስትሪ ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ይደረጋል፤
 ስልጠናው ፕሮጀክትን መሰረት ያደረገ ነው፤
 ከስልጠናው ጎን ለጎን ሰልጣኞች ቁጠባ እንዲቆጥቡ ይደረጋል፤ ከዚያም ቅድመ-ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰረቱ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
 ከ1994 ዓ.ም (ሙሉ በሙሉ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ) እስካሁን ድረስ ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች በበርካታ የሙያ አይነቶች በቀንና በማታ ፕሮግራም ተመርቀው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች ስራ-አጥ ወገኖች የስራ እድል ፈጣሪ መሆን የቻሉ ዜጎችን አስመርቋል፡፡
 ከምረቃ በኋላ ሰልጣኞች ያሉበትን የስራ ሁኔታ በማጥናት ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡
 ለደንበኞች በሚሰጠው አገልግሎት የISO 9001:2008 ስታንዳርዶችን ያሟላ በመሆኑ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አማካኝነት የጥራት ስራ አመራር ማረጋገጫ በ2006 ዓ.ም አግኝቷል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስታንዳርዱን ማስጠበቁን በኤጄንሲው በኩል ሰርቬይላንስ ኦዲት በየዓመቱ ተካሂዶ ማረጋገጫ ተሰጥቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የኮሌጁ አገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርዶችን ያሟላ መሆኑን ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ISO 19011:2015ን አሰራርን የዘረጋ ሲሆን የማረጋገጫ ሰርቲፊኬቱን ለማግኘት በሂደት ላይ ነው፡፡
 ከተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት ተግባራዊ አድርጓል፡፡
 የካይዘን ፍልስፍና ወደሀገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የስልጠና ሾፖችና የስራ ክፍሎች በካይዘን እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡
 በተመሳሳይ ሌላኛውና ትልቁ ተልዕኮው ደግሞ የደንበኞቹን እና የአካባቢውን መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጅ ፍላጎት መሰረት ያደረገ የምርትና ማምረቻ ቴክኖሎጅ በማላመድ እና በፈጠራ በመስራት፤ ብሎም በማሸጋገር ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
 በተለያዩ የስራ መስኮች ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአራቱም የድጋፍ ማዕቀፎች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት የአሰራር፣ የክህሎት፣ የአመለካከት እና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ ከማድረግ አልፎ ወደመካከለኛ የኢንዱስትሪነት እንዲያድጉ የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው፡፡
 የአሰልጣኝ መምህራንንና የአስተዳደር ሰራተኛውን አቅም ለመገንባት የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና ያመቻቻል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የማሰልጠኛ ማሽኖችና ግብዓቶችን በመግዛት፣ ወርክሾፖችን በመገንባት የራሱን አቅም እየገነባ ነው፡፡
 በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የመሆን ዋነኛ ዓላማ አለው፡፡
 ኮሌጁ ከዋና ዋና ተልዕኮዎቹ ጎን ለጎን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ማህበራዊ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ መካከል በቅርቡ ለክፍለ-ከተሞች ከ300 በላይ የአዳራሽ ወንበሮች፣ በርካታ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩና በአዳዲስ የተተኩ ኮምፒዩተሮች፣ ለአቻ ተቋማት (ኮሌጆች) የጋርመንትና ቴክስታይል ማሽኖች እና ያገለገሉ ኮምፒዩተሮች እንዲሁም አንድ የመስክ መኪና፣ ለአረጋዊያን በየዓመቱ የተደረገ የአልባሳት ድጋፍ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከስታፉ እና ከኮሌጁ የተደረገ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ፣ ለ5 ኅፃናት በፀረ-ኤድስ ፈንድ በየወሩ ቋሚ የገንዘብ ድጋፍ እና በየ6 ወሩ ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ባለፉት 4 ዓመታት ብቻ የተደረጉ ድጋፎች ናቸው፡፡

የቅሬታ ሰሚ አተገባበር እና ተግባራዊነትን በተመለከተ ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ስልጠና ተሰጠ፡፡ደሴ፡- ሰኔ 15 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)በወይዘሮ ስኂና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቅሬታ ሰሚ አተ...
22/06/2026

የቅሬታ ሰሚ አተገባበር እና ተግባራዊነትን በተመለከተ ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ስልጠና ተሰጠ፡፡

ደሴ፡- ሰኔ 15 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)

በወይዘሮ ስኂና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቅሬታ ሰሚ አተገባበር እና ተግባራዊነትን በተመለከተ ለኮሌጁ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በEASE (Education and Skill For Employability) ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የEASE ፕሮጀክት የአካባቢና ማህበራዊ ጥበቃ (Environment & Social Safeguard) አስተባባሪ እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ መሃመድ ሲሆኑ፣ በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ቅሬታዎች ቢፈጠሩ ሊከተሉ ስለሚገባቸው የቅሬታ አፈታት (Grievance Redress Mechanism) ሂደቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አስተባባሪው አክለውም እስካሁን በፕሮጀክቱ ዙሪያ የተነሱ ቅሬታዎች ምን ምን እንደነበሩና በተግባር የተፈቱበትን ስኬታማ መንገድ ለኮሚቴው አባላት አስታውሰዋል፡፡

በስልጠናው ወቅት የስነ-ምግባር ደንብ፣የአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሁም በEASE ፕሮጀክት አማካኝነት በስርዓተ-ፆታ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም በሴቶች አቅም ግንባታ ዙሪያ ወደፊት በርካታ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱንም ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላቱ በEASE ፕሮጀክት ድጋፍ በኮሌጁ ግቢ ውስጥ ለሴት ሰልጣኞች ማረፊያና (Female Trainees Wellness center) የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገለግሉ ተለይተው የተዘጋጁትን ክፍሎች በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡

የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስራና ተግባር ስርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡ ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ) የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትም...
20/06/2026

የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስራና ተግባር ስርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡

ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)

የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዲሱ የስራና ተግባር ስርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብነው ደሳለኝ፤ የቀድሞው ስርዓተ ትምህርት ይዘት በጽንሰ-ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ተማሪዎችን ለፈጠራ የሚያነሳሳ እንዳልነበረ አስታውሰዋል። በአንጻሩ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ከጽንሰ-ሃሳብ ባለፈ በተግባራዊ ልምምድ ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ተማሪዎችን ለስራ ፈጠራ የሚያነሳሳና የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።

ርዕሰ መምህሩ አክለውም ተማሪዎቹ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ከመርዳት ጀምሮ ለስልጠናው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በበኩላቸው፣ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ገና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የሙያ ትምህርት እንዲወስዱ የሚያበረታታ በመሆኑ፣ የፈጠራ ችሎታና ክህሎት ላላቸው ተማሪዎች ትልቅ አጋዥና በር ከፋች መሆኑን አስገንዝበዋል። አቶ ፍቅር አያይዘውም ወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በከተማዋ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሙያ ትምህርቱ ውጤታማ ይሆን ዘንድ እያደረገ ላለው ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሌላው በምረቃው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር፣ ኮሌጁ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያሳለፋቸውን የስኬት ጉዞዎች ያወሱ ሲሆን፤ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሰልጣኞችን በብቁ ክህሎትና እውቀት አንጸው "ከታዛዥነት ወደ አዛዥነት" (ወደ ስራ ፈጣሪነት) የሚቀይሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም ወጣቶች የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ቀዳሚ ምርጫቸው እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የሙያ ትምህርት ስልጠና በአራት ዋና ዋና የስልጠና ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ እነሱም፡ጋዜጠኝነት፣የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት፣አካውንቲንግና ፋይናንስ እንዲሁምኮምፒውተር ሳይንስ ናቸው፡፡

በደሴ ከተማ በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአጫጭር ስልጠና ምረቃ ስነ-ስርዓት ተከናወነ፡፡ ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)  የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ...
20/06/2026

በደሴ ከተማ በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአጫጭር ስልጠና ምረቃ ስነ-ስርዓት ተከናወነ፡፡

ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከ «3R-4 CACE» ፕሮጀክት ጋር በመተባበር፣ በወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የስራ ክህሎት ዘርፎች ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ሴቶችና እናቶችን ዛሬ በድምቀት አስመርቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ አስተዳደር ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀሰን አበጋዝ ሰልጣኞቹ ከ10 እስከ 45 ቀናት በቆየው በዚህ ተግባራዊ ስልጠና ላይ በቂ እውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ገልጸዋል። ይህ ያገኙት እውቀትም በቀጣይ ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ ትልቅ አጋዥ ሊሆናቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር በበኩላቸው፣ ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በቂ እውቀት እንዳገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ስልጠና ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ፕሮጀክቱ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችንና ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ያሟላ መሆኑ እንዲሁም ሰልጣኞቹ በሙሉ ሴቶች መሆናቸውና ስልጠናውን ደግሞ በሴት ባለውለታ ስም በተሰየመው አንጋፋው የወ/ሮ ስኂን ተቋም ውስጥ መከታተላቸው ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል።

ዲኑ አክለውም፣ ኮሌጁ ስልጠና በመስጠት ብቻ እንደማይወሰንና ተመራቂዎቹ ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

ስልጠናው በግብርናው ዘርፍ፡ የዶሮ እርባታ፣ የፍየልና በግ እርባታ እንዲሁም እንስሳት ማድለብ፣ በአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግና ኢንደስትሪ፡ የልብስ ስፌት እና የላርጎ (ፈሳሽ ሳሙና) ማምረት እንዲሁምበአገልግሎት ዘርፍ፡- የምግብ ዝግጅት ስልጠናዎች ይገኙበታል፡፡

ይህ በሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ እና በ «3R-4 CACE» ፕሮጀክት ትብብር የተካሄደው የስራ ክህሎት ስልጠና፣ የምረቃው ባለቤት የሆኑትን እናቶችና ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉና በከተማዋ ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

በወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በEASE ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የትምህርት ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፡፡ ደሴ፡- ሰኔ 12 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ) በወይዘሮ ስህና ፖሊቴክኒክ...
19/06/2026

በወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በEASE ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የትምህርት ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ደሴ፡- ሰኔ 12 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)

በወይዘሮ ስህና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በEASE (Education and Skill For Employability) ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የትምህርት ክፍሎች የተዘጋጀ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል። ይህ ስልጠና በዋናነት ለጋርመንት፣ ለኤሌክትሪክ ሲቲ እና ለአይሲቲ (ICT) የትምህርት ክፍሎች የተሰጠ ሲሆን፣ ዓላማውም ፕሮጀክቱ እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን ግልጽ ለማድረግ ነው።

ስልጠናው በEASE ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ጥበቃ (Environment & Social Safeguard) አስተባባሪ የሆኑት አቶ መላኩ መሃመድ በስልጠናው ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። አስተባባሪው በንግግራቸው የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓላማና አተገባበር ያብራሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ አማካኝነት እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ስራዎችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

አቶ መላኩ አያይዘውም በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ቅሬታዎች ቢፈጠሩ ሊከተሉ ስለሚገባው የቅሬታ አፈታት ሂደት Grievance Redress Mechanism (GRM) እና ስለ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው አሰራር ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል። በተጨማሪም፡የስነ-ምግባር ደንብ፡ ፕሮጀክቱ የሚከተለውን ጥብቅ የስነ-ምግባር መመሪያ ፣ የስራ ላይ ስለሚደረግ የደህንነት አጠባበቅ Occupational Health and Safety (OHS)፣ ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጥ ትኩረት እንዲሁም በስራዎች ሳቢያ በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ለመቀነስ የተነደፉ ልዩ የአካባቢ ጥበቃ ስልቶችን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።

በተመሳሳይም በዕለቱ የፕሮጀክቱ የስርዓተ-ፆታ ፎካል (Gender Focal person) የሆኑት ወይዘሮ ገነት መላኩ በበኩላቸው በስርዓተ-ፆታ ዙሪያ Gender Based Violence(GBV)እና በEASE ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ወይዘሮ ገነት በስልጠናው ወቅት በሴቶች አቅም ግንባታ፣ በፕሮጀክቱ ድጋፍ በኮሌጁ ግቢ በሴቶች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ያሉትን ስራዎች አንስተዋል።

ይህ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና በኮሌጁ የEASE ፕሮጀክት ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ፣ ግልጽነት የተሞላባቸው እና ማህበራዊና አካባቢያዊ ኃላፊነትን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይታሰባል፡፡

ማስታወቂያ
17/06/2026

ማስታወቂያ

የሴቶችና እናቶችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለመ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ደሴ፡-ሰኔ 9 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)በደሴ ከተማ የሴቶችና የእናቶችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋ...
16/06/2026

የሴቶችና እናቶችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለመ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

ደሴ፡-ሰኔ 9 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)

በደሴ ከተማ የሴቶችና የእናቶችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ስልጠናው የ3R-4 ፕሮጀክት ከወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ስልጠናው በግብርናው ዘርፍ፡ የዶሮ እርባታ፣ የፍየልና በግ እርባታ እንዲሁም እንስሳት ማድለብ፣ በአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግና ኢንደስትሪ፡ የልብስ ስፌት እና የላርጎ (ፈሳሽ ሳሙና) ማምረት እንዲሁምበአገልግሎት ዘርፍ፡- የምግብ ዝግጅት ስልጠናዎች ይገኙበታል፡፡

ይህ እንደየዘርፉ ባህሪ ከ10 እስከ 45 ቀናት የሚቆይ የክህሎት ስልጠና፣ እናቶችና ሴቶች ራሳቸውን ችለው ወደ ስራ እንዲገቡና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሙያ ብቃት ምዘና በመሰጠት ላይ ነውደሴ፡-ሰኔ 5 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)
12/06/2026

በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሙያ ብቃት ምዘና በመሰጠት ላይ ነው
ደሴ፡-ሰኔ 5 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)

ለወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኞች የISO 9001:2015 የጥራት አመራር ስርዓት እና የውስጥ ጥራት ኦዲትን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ:: ደሴ፡-ሰኔ 3 /2018ዓ.ም...
10/06/2026

ለወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኞች የISO 9001:2015 የጥራት አመራር ስርዓት እና የውስጥ ጥራት ኦዲትን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ::

ደሴ፡-ሰኔ 3 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)

የወይዘሮ ስኂን ፖቴክኒክ ኮሌጅ የISO 9001:2015 የጥራት ስራ አመራር ስርዓትን አስመልክቶ ለሰራተኞች የተዘጋጀ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናው Education and Skill for Employment Project (EASE) ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት የሚሰጥ ነው፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር እንደገለጹት የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ ሰራተኛው ተቋማዊ የጥራት መርሆዎችን ጠብቆ እንዲሰራ ለማንቃትና ለማስታወስ ነው፡፡ ኮሌጁ በበጀት ዓመቱ ለሚጠብቀው ዓለም አቀፍ የክትትል ኦዲት (Surveillance Audit) ብቁ ዝግጅት ማድረግ እንዲችል የሰራተኛው ግንዛቤ መታደስ ወሳኝ መሆኑንም ዲኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይህ ስልጠና ተቋማችን ቀደም ሲል ያገኘውን የISO 9001:2015 ዕውቅና ይዞ ለመቀጠልና ለሚመጣው የክትትል ኦዲት ራሱን በሚገባ ለማዘጋጀት ትልቅ ዕድል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ሰራተኛው ከዚህ በፊት የነበረውን ግንዛቤ በማደስ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰልጣኝ ስልጠናውን በትኩረትና በሃላፊነት ስሜት ሊከታተለው እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ስልጠናው በውስጥ ጥራት ቁጥጥር ክፍል የተሰጠ ሲሆን ከISO 9001:2015 የጥራት አመራር ስርዓት በተጨማሪ ሶስት ማንዋሎች ላይ ማለትም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የጥራት ማረጋገጫ መስፈርቶች መመዘኛና መገምገሚያ ማንዋል ፣ሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን እንዲሁም ዲጂታል ላይብረሪ የሚሉት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአይሲቲ የስልጠና ዘርፍ የሚሰለጥኑ የ2018 ዓ.ም የቀን ተመራቂ ተማሪዎች የሰሩትን የተለያዩ ፕሮጀክት  ለመምህራቸው ገለፃ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል፡-
08/06/2026

የወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአይሲቲ የስልጠና ዘርፍ የሚሰለጥኑ የ2018 ዓ.ም የቀን ተመራቂ ተማሪዎች የሰሩትን የተለያዩ ፕሮጀክት ለመምህራቸው ገለፃ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል፡-

Address

Dessie
54

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Woizero Siheen Polytechnic College posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The University

Send a message to Woizero Siheen Polytechnic College:

Share